ዓባይ ባንክ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

ዓባይ ባንክ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

ዓባይ ባንክ አ.ማ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኤሌክትሮኒክስ ግብር አሰባሰብ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የኋላ ገሠሠ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አቶ የኋላ ገሠሠ እንደተናገሩት የዓባይ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት እየጎለበተና እየዘመነ መምጣቱን ገልጸው፣ ደንበኞች በተዘረጋው የኤሌክትሮኒክ ግብር ማሰባሰቢያ ዘዴ በመጠቀም ክፍያቸውን በዓባይ ባንክ በኩል እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ የኋላ አክለውም ዓባይ ባንክ በየዓመቱ ከሚያገኘው ገቢ ላይ ከፍተኛ ታክስ በመክፈል በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ወ/ሮ አይናለም በበኩላቸው የባንክ ደንበኞች የታክስ ክፍያቸውን ለመፈጸም የተዘጋጀውን ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓት ቢጠቀሙ ፈጣን፣ አስተማማኝ እና ጊዜ ቆጣቢ በመሆኑ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስተማማኝ የሳይበር ጥበቃ በማድረግ የታክስ ክፍያ ሥርዓቱ እንዲሳለጥ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣና ከባንኮችና ገቢዎች ሚኒስቴር ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዓባይ ባንክ ቀደም ሲል በዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቱ የፐብሊክ ትርንስፖርት ክፍያ፣ የአውሮፕላን ጉዞ ቲኬት ክፍያ፣ የቴሌ ብር እና ሌሎችንም ዘመናዊ አሰራሮች ወደ ሥራ በማስገባት ለደንበኞቹ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.