አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24/2014 – የዓባይ ባንክ ሠራተኞች ዓለምአቀፍ የኦቲዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀንን ምክንያት በማድረግ የነህሚያ ኦቲዝም ማዕከልን ጎበኙ፡፡

በጉብኝቱ ላይ የባንኩ ስትራቴጂና ማርኬቲንግ ዋና መኮንን አቶ ወንድይፍራው ታደሰ እና ሌሎች የባንኩ ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን፣ ከጉብኝቱ በተጨማሪ ለማዕከሉ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

አቶ ወንድይፍራው ታደሰ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት ዓባይ ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ሁልጊዜ አጋር መሆኑን ጠቅሰው፣ ህብረተሰቡ ኦቲዝምን በተመለከተ ያለውን ግንዛቤ እንዲያዳብር እና ኦቲዝም ላለባቸው ልጆች ትኩረት በመስጠት ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረከክት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የነህምያ ኦቲዝም ማዕከል መሥራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ራሔል ዓባይነህ በበኩላቸው የዓባይ ባንክ ሠራተኞች ማዕከሉን በቦታው ተገኝተው በመጎብኘት ያሳዩት ፍቅርና አጋርነት እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ለተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የነህሚያ ኦቲዝም ማዕከል በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የኦቲዝም ማዕከሎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የተመሰረተው ሰኔ 9 ቀን 2003 ዓ.ም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ከ60 በላይ የሚሆኑ ታዳጊ ሕፃናት ክትትልና ድጋፍ ያገኛሉ፡፡

ባንኩ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች ለተቸገሩ ወገኖች እና ተቋማት ትርጉም ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግ የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርቡ በባንክ ሠራተኞች መዋጮ በሰሜን ወሎ ዋግህምራ እና ሰቆጣ አካባቢዎች በድርቅና ረሀብ ለተጎዱ ወገኖች አራት ሚሊየን ብር የሚገመት የስንዴ ዱቄት መለገሳቸው ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.