በክሪፕቶ ከረንሲ መገበያየት በሕግ ያስጠይቃል

በክሪፕቶ ከረንሲ መገበያየት በሕግ ያስጠይቃል

በኢትዮጵያ በክሪፕቶ ከረንሲ ክፍያ መፈጸም ወይም መገበያየት በብሔራዊ ባንክ እውቅና ያልተሰጠው በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከሕገወጥ ተግባር ራሱን እንዲጠብቅ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

የኢትዮጵያ የገንዘብ መደብ ብር እንደሆነና በብሔራዊ ባንክ በሌላ አኳኋን ካልተፈቀደ በስተቀር በሀገሪቱ የሚከናወኑ ማናቸውም የገንዘብ ግንኙነቶች ሁሉ የሚከፈሉት በብር እንደሚሆን የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 በግልጽ መደንገጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 መሠረት በየትኛውም የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድም ሆነ ሥርዓት ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ገንዘብ ነክ አገልግሎት መስጠት አይቻልም፡፡

ነገር ግን ከጥናት ለመረዳት እንደተቻለው በአሁኑ ወቅት ከህግ እውቅና ውጪ የክሪፕቶ ከረንሲ፣ እንደ ቢትኮይን እና የመሳሰሉት የምናባዊ ንብረት (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) አገልግሎት በኢትዮጵያ እየተስፋፉ መምጣታቸውን ባንኩ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ይህ ተግባር ከብሔራዊ ባንኩ እውቅና ወጪ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበት እና በተለይም በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ለማሸሽ ምቹ ሁኔታዎች እየፈጠረ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

ምናባዊ ንብረትን ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገወጥ ተግባር እራሱን መጠበቅ ይኖርበታል ብሏል ባንኩ፡፡

በመሆኑም ይህን ፈጽመው በሚገኙ አካላት ላይ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጾ፣ ኅብረተሰቡም ይህን ሕገወጥ ተግባር የሚሰሩ አካላትን ሲመለከት ለብሔራዊ ባንክና ለሚመለከታቸው ሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.