የቦርድ ሊቀመንበር መልዕክት

ውድ የባንካችን ባለአክሲዮኖች፣

 

የባንካችንን የ2015 ዓ.ም ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ሳቀርብላችሁ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡

ያለፈው ዓመት በርካታ ተግዳሮቶችና ዓለምአቀፍ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ያስተናገደ ዓመት ነበር፡፡ መቋጫ የታጣለት የራሺያና ዩክሬይን ግጭት እንዲሁም ታይዋንን ማዕከል በማድረግ ተባብሶ የቀጠለው የቻይና እና የአሜሪካ ፍጥጫ እንዲሁም በበርካታ ሰብዓዊ ፍጡራን ላይ ጫና ያሳደረው የአየር ጠባይ ለውጥ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ዋነኛ መገለጫዎች ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ዓመቱ በፍላጐት እና አቅርቦት አለመጣጣም ምክንያት የተከሰተው ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት መሻሻል ያልታየበት ሆኖ አልፏል፡፡ ምንም እንኳን መንግስታት የኮቪድ-19ን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም የተገበሩት የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ አቅርቦቱን የተገዳደረ ቢሆንም የአቅርቦት ሰንሰለቱ የራሺያ-ዩክሬን ግጭት እስከ ተከሰተበት ወቅት ድረስ ወደ ቅድመ ኮቪድ-19 ደረጃው በመመለስ መሻሻል ያሳየ ሁነት ነበር፡፡

በዓመቱ ውስጥ እነዚህን የመሳሰሉ ተግዳሮቶችና ተፅዕኖዎች የታዩ ቢሆንም የዓለም ጤና ድርጅት ዓለማችን ከወረርሽኙ ዳፋ እየተላቀቀች መሆኑን መግለጹ እንደመልካም አመላካች የሚታይ ነው፡፡

በሌላ በኩል ቻይና እና ብራዚል በየራሳቸው የመገበያያ ገንዘብ የንግድ ልውውጥ ለማካሄድ ስምምነት ላይ መድረሳቸው በዓመቱ ከተከሰቱ አበይት ጉዳዮች መካከል ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡

እ.ኤ.አ. የ2022 የተመዘገበው የ3.5 በመቶ ዓለምአቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ከቀደሙት ዓመታት አማካይ ዝቅ ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያው እ.ኤ.አ. በ 2023 ወደ 3 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል አመላክቷል፡፡ ከግጭቶች፣ ከሸቀጦች ዋጋ ንረት፣ ከአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ከውጭ ዕዳ ሸክም ጋር የሚታገሉት የአፍሪካ ሀገሮችም ተመሳሳይ ተግዳሮቶችን ተጋፍጠዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለት ዓመት ካስቆጠረው የሰሜኑ ግጭት ወጥታ ሰላምና መረጋጋት ላይ ትገኛለች፡፡ በመሆኑም የኢኮኖሚ ዕድገቱ ከባለፈው ዓመት የ6.4 በመቶ ምጣኔ አንፃር መሻሻልን አሳይቶ የ7.5 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

በአንጻሩ ባንካችን እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች ተቋቁሞ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በዚህም መሰረት ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ የ29 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት በማስመዝገብ ብር 41.8 ቢሊዮን ደርሷል፡፡

የደንበኞቹን ቁጥርም የ49 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት በማሳየት በዓመቱ መጨረሻ ላይ 2.5 ሚሊዮን ያደረሰ ሲሆን የአገልግሎት ተደራሽነቱን በማስፋት በበጀት ዓመቱ 110 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ትርፋማነቱን ብር 2.1 ቢሊዮን በማድረስ ባንኩን ወደ አዲስ ከፍታ መውሰድ ተችሏል፡፡

በቀጣይም ለተሻለ ዕድገትና ለዘላቂ ውጤታማነት የሚያበቃ አዲስ መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ረገድ ሰፊ ተቋማዊ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሰረት Aጉዞ ከፍታ” በሚል ስያሜ ከ 2016 እስከ 2021 ድረስ ሥራ ላይ የሚውል አዲስ የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ባንካችን Aቀዳሚ ተመራጭ ባንክ መሆን” የሚል ራዕይ ሰንቆ Aየላቀ የባንክ አገልግሎት በመስጠት የባለድርሻ አካላትን ዕሴት የማሳደግ” ተልዕኮ በማንገብ ጉዞውን ጀምሯል፡፡ ይህን ተከትሎም አዲስ የመዋቅር ጥናት የተተገበረ ሲሆን የባንካችንን ብራንድ መገለጫዎች የማሻሻል ወሳኝ ፕሮጀክትም በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

በቀጣይም በተግዳሮቶች ሳንገታ ላስቀመጥናቸው ግቦች መሳካት ጠንክረን በመሥራት በሙያዊ ጥረት እና በሙሉ ትኩረት በመንቀሳቀስ የሚገጥሙንን መሰናክሎች ማለፍ እንደምንችል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

በመጨረሻም የሥራ ጊዜያቸውን በስኬት በማጠናቀቅ ለተሰናበቱ እንዲሁም ለተረካቢው የቦርድ አባለት ላበረከቱት የላቀ የአመራር እና ክትትል አስተዋጽኦ ከልብ ማመስገን እወዳለሁ፡፡ ለሥራ አመራር አባላትና ለታታሪ ሠራተኞቻችን በሙሉ እንዲሁም ሁሌም ከጐናችን ላሉት ውድ ደንበኞቻችን አድናቆቴን ከምስጋና ጋር መግለጽ እወዳለሁ፡፡ በስራችን ሁሉ ለተባበሩን የመንግስት ተቋማት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን የተረጋጋ በማድረግ ረገድ ለነበራቸው ወሳኝ ሚና በተለየ መልኩ ማመስገን እወዳለሁ፡፡

 

አመሰግናለሁ!

አምላኩ አስረስ (ዶ/ር)

የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር