አንድ-ብር ለአንድ-ዶላር

ዓባይ ባንክ ወደ ሀገራቸው በመምጣት ላይ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በሙሉ እንኳን ወደ እናት ሀገራችሁ ደህና መጣችሁ በማለት መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

ባንካችን ለመንግስት ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ወደሀገር ቤት በመግባት ላይ ላሉ አንድ-ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በጠቅላላ ልባዊ ሰላምታውን ማቅረብ ይወዳል፡፡

ይህንን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ በዓለም ዙሪያ፣ በተለያዩ ሀገራት ካሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ወደሀገር ቤት የመምጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ የተጀመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መጠነ-ሠፊ እና ዘርፈ-ብዙ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል እና የመስተንግዶ ዝግጅቶች በተለያዩ ባለድርሻ አካለት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ ታላቁ ወደ ሀገር ቤት ጉዞ ይበልጥ ጠንካራ ኢትዮጵያን ከመገንባት አኳያ በርካታ መልካም ገጽታዎችና ቱሩፋቶች እንደሚኖሩት ይታመናል፡፡  በልጆቿ መልካም እና ለጋስ እጆች አማካኝነት በሀገሪቱ አጠቃላይ ልማትና የተጎዱትን በመደገፍ ረገድ በሚደረጉ አበይት ጉዳዮች ዙሪያ አዎንታዊ እንቅስቃሴዎች ይከናወናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዋናነት ግን የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት የሀገራቸውን አሁናዊ ችግሮች በመቅረፍ ዙሪያ አሻራቸውን ማሳረፍ የሚችሉባቸው ሁለት አበይት ቁምነገሮች ይታያሉ፡- ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በተለያየ መልኩ መደገፍ እና በእጃቸው የሚገኘውን የውጭ ሀገር ገንዘብ ህጋዊ በሆነው የባንክ ሥርዓት በመመንዘር የሀገራችንን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከማሻሻል አንጻር ዓይነተኛ ሚና መጫወት ይሆናሉ፡፡

ዓባይ ባንክ የቀረበው የአንድ-ብር ለአንድ-ዶላር ቅስቀሳም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ወደሀገር ቤት የመጡበትን ዋና ዓላማ ማለትም የተጎዱ ወገኖቻችንን ከመደገፍ እና መልሶ ከማቋቋም አንጻር የታሰበ ነው፡፡

ዓባይ ባንክ ያቀረበው ይህ ቅስቀሳ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች አንድ ብር ከእያንዳንዱ የውጭ ምንዛሪ ግዥ / ዶላር ዕርዳታ ማሰባሰብን ያለመ ነው፡፡  በዚሁም መሠረት፣ እንደምሳሌ፣ አንድ የዳያስፖራ እንግዳችን በየትኛዉም በባንካችን ከ330 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎቻችን በመገኘት 500 ዶላር የመነዘረ እንደሆነ ዓባይ ባንክ 500 ብር ወዲያዉኑ ለተጎዱ ወገኖቻችን ድጋፍ እንዲውል በተለየ መልኩ ያስቀምጣል ማለት ነው፡፡

በዚህ መልኩ የሚዋጣው ገንዘብም ከፍተኛ እንደሚሆን እና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዕርዳታ ፈላጊ ወገኖች ትርጉም ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የተወደዳችሁ የዳየስፖራ እንግዶቻችን፤ ይህ የአንድ ብር ለአንድ ዶላር ቅስቀሳ እናንተ ላይ ምንም ዓይነት የምንዛሪ ቅናሽ በማያስከትል መልኩ በዕለቱ በሚኖረው ኦፊሴላዊ መደበኛ የውጭ ምንዛሬ ተመን መሠረት የሚከናወን ነው፡፡  ነገር ግን፣ በዓባይ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት በመጠቀማችሁ ብቻ ባንኩ ከራሱ ወጪ አንድ ብር በእያንዳንዱ ዶላር/የውጭ ሀገር ገንዘብ ለተጎዱ ወገኖች መደገፊያ ያውላል ማለት ነው፡፡

ዓባይ ባንክ እናንተን በማገልገሉ፣ ሀገራችሁንና ወገናችሁንም እንድትደግፉ በማገዙ እንዲሁም የራሱንም ተቋማዊ ማኅበራዊ ኃላፊነት በመወጣቱ ኩራት ይሰማዋል፡፡

ዓባይ፣ ታማኝ አገልጋይ !

Leave a Reply

Your email address will not be published.