ዓባይ ባንክ ለ5ኛው ዙር “ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” ፕሮግራም አሸናፊዎች ሽልማት አስረከበ

ዓባይ ባንክ ለ5ኛው ዙር “ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” ፕሮግራም አሸናፊዎች ሽልማት አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28/2014 – ዓባይ ባንክ አ.ማ. ለ5ኛው ዙር የ“ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” ፕሮግራም አሸናፊዎች የሽልማት አሰጣጥ ሥነሥርዓት ዛሬ አከናውኗል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ የኋላ ገሠሠ እንደገለጹት በባንኩ የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት መጠቀም መቻል ሕገወጥ የገንዘብ ምንዛሬን ለመከላከል ያግዛል፤ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መጎልበት የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ እንዲሁም ደንበኞች ባንኩ የሚሰጣቸውን በርካታ አገልግሎቶች እንዲላመዱ ዕድል ይሰጣል ብለዋል፡፡     

ባለፉት አስራአንድ ዓመታት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን ዋና ሥራ አሰፈጻሚው ገልጸው፣ ደንበኞች ለባንኩ ዕድገት እያበረከቱት ካለው አስተዋጽኦ አንጻር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይህ የ5ኛ የሽልማት ፕሮግራም መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡   

የዕጣው አሸናፊዎች የባንኩ አምባሳደሮች መሆናቸውን ገልጸው፣ ለዕድለኞች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡     

የዓባይ ባንክ “ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” ፕሮግራም እንደሚቀጥልና ደንበኞች ባንኩ በሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቶ የኋላ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ 

በ1ኛ ዕጣ ቁጥር 2672 የዘመናዊ ሱዙኪ ዲዛየር አውቶሞቢል አሸናፊ የሆኑት ወ/ሮ እመቤት አድነው በበኩላቸው ከአሜሪካን ሰሜን ካሮላይና ግዛት ከወንድማቸው የተላከላቸውን የአሜሪካን ዶላር በዓባይ ባንክ በመመንዘራቸው ዕጣ ውስጥ እንደገቡና አሸናፊ እንደሆኑ አስታውሰው፣ ዕድለኛ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡    

በቀጣይም ከዓባይ ባንክ ጋር በመስራት የጠበቀ ቁርኝት እንደሚፈጥሩ ገልጸው፣ ባንኩ ቃሉን ጠባቂ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ዓባይ ባንክ በ1ኛ ዕጣ ሱዙኪ ዲዛየር ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል፣ 2ኛ ዕጣ አምስት ከ 200-350 ሊትር የሚይዙ ሳምሰንግ ፍሪጆች፣ 3ኛ ዕጣ አምስት ሳምሰንግ 32 ኢንች ቴሌቪዥኖች፣ 4ኛ ዕጣ አምስት ኤችፒ ላፕቶፖች እና 5ኛ ዕጣ አስር ሁዋዌ የሞባይል ቀፎዎች ለዕጣ አሸናፊ ዕድለኞች ቀርበዋል፡፡ 

በዛሬው ዕለት ሽልማት አሰጣጥ ፕሮግራም የተካሄደው ለአዲስ አበባ አሸናፊዎች ሲሆን፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ አሸናፊዎች ደግሞ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ታዛቢዎች በሚገኙበት ሽልማቱን የሚያስረክብ ይሆናል፡፡  

ዓባይ ባንክ ከታህሳስ 20/2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 19/2014 ዓ.ም ድረስ ሲያከናውን የቆየው 5ኛ ዙር የ“ይመንዝሩ፣ ይቀበሉ፣ ይሸለሙ” ፕሮግራም የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ቀደም ሲል በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አዳራሽ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

    

   

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.