የቦርድ ሊቀመንበር መልዕክት

የተከበራችሁ የባንካችን ባለአክሲዮኖች፣

ከሁሉ አስቀድሜ፣ በተስፋ ጥላ ስር እየመራን ለዛሬዋ ቀን ላደረሰን ፈጣሪ ታላቅ ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ ከዚህም በመቀጠል የባንካችንን የ2014 ዓ.ም ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ሳቀርብላችሁ ከፍተኛ ደሰታ ይሰማኛል፡፡

የኮቪድ ክትባት በቶሎ መገኘት እና ፈጣን ስርጭት እንዲሁም በሀገራት እና ተቋማት ከተወሰዱ መጠነ-ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ርምጃዎች ጋር በተያያዘ ዓለምአቀፉ ኢኮኖሚ ማንሰራራት ጀምሯል፡፡  ይሁን እንጂ፤ አዲሱ የኮቪድ-19 ልውጥ የኦሚክሮን ቫይረስ በዓመቱ አጋማሽ ላይ መከሰት እንዲሁም የራሺያ-ዩክሬይን ግጭት በበጀት ዓመቱ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ መቀስቀሱ በማንሰራራት ላይ ለነበረው ኢኮኖሚ አሉታዊ ተጽዕኖው ተግዳሮት ሆኖበት ታይቷል፡፡ ዓለማችን ከከፍተኛ የምግብ-ነክና ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንዲሁም የምግብ እና ሸቀጦች አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ ዳግም ተግዳሮቶችን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

በምግብ ራስን የመቻል ችግር በተለያዩ የአፍሪካ አካባቢዎች ሲታይ የቆዬ ሲሆን  ይልቁኑም  እንደ ሶማሊያ ባሉ ከጥቁር ባሕር ሀገራት በሚገቡ የምግብ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጥገኛ በሆኑ ሀገራት ላይ ክፉኛ ጉዳት አድርሷል፡፡  ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንዴን በርከት ካሉ ሀገራት ከማስገባቷ ጋር ተያይዞ እንዲሁም በሀገር ውስጥ እየታየ ያለው አመርቂ የስንዴ ምርት እድገት ሁኔታውን የተሻለ ቢያስመስለውም በሀገራችን እስካሁን እየታየ የሚገኘው የተራዘመ እና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ዜጎችን ለከፋ ሁኔታ እየዳረገ ይገኛል፡፡

በዚህም ምክንያት ከተከሰተው ዋጋ ንረት በተጨማሪ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ካለው ጦርነትም ጋር በተያያዘ በሀገራችንም ያለው አጠቃላይ ሁኔታ እምብዛም የተሻሻለ አይመስልም፡፡

በምስረታ ላይ የነበሩ በርካታ አዳዲስ ባንኮች ስራ መጀመራቸውን ተከትሎ የባንክ ኢንዱስትሪው በሚታይ ሁኔታ ሰፍቷል፡፡  ለውጭ ባንኮች ዘርፉን ክፍት ከማድረግም አንጻር መንግስት ግልጽ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን ባንክ-ነክ ያልሆኑ እንደ ኢትዮ-ቴሌኮም ያሉ ተቋማት በቴሌብር መልክ ወደዘርፉ መግባትም በዘርፉ እየታየ ያለውን ውድድር ይልቁኑም ከፍ ወዳለ ደረጃ እያሸጋገረው ይገኛል፡፡

ከሰሜኑ ግጭት ጋር በተያያዘ 25% የሚሆኑ የባንካችን ቅርንጫፎች ለስድስት ወር ያህል አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ነበር፡፡  ይሁንና የደረሱትን ጉዳቶች በመጠገን እንዲሁም የጠፉና ከጥቅም ውጭ የሆኑ ንብረቶችን በመተካት በሚቻለው ፍጥነት ቅርንጫፎቹን ወደስራ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

ምንም እንኳን ነባራዊ ሁኔታው ለስራ ምቹ ከባቢ የፈጠረ ባይሆንም ባንካችን ከበርካታ መለኪያዎች አንጻር በዓመቱ ጥሩ የሚባል ውጤት አስመዝግቧል፡፡  ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ  ባንካችን በዓመቱ ብር 8.5 ቢሊዮን ተጨማሪ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን ይህም የ35% ዕድገት እንደነበረው ያመለክታል፡ ፡  ለዚህም አጥጋቢ ውጤት መመዝገብ የቅርንጫፍ ማስፋፋት ስራው በዋናነት ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡ በዓመቱ ውስጥ 87 አዳዲስ ቅርንጫፎች የተከፈቱ ሲሆን ጠቅላላ ብዛታቸውም የ30% ዓመታዊ ዕድገት በማስመዝገብ 373 ደርሷል፡፡    ከዚህም ጎን ለጎን ባንካችን የዋናውን መ/ቤት ሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክት በዋና ከተማዋ እምብርት ላይ ማስገንባት ጀምሯል፡፡  ከዚህም በተጨማሪ የዲዛይን ስራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ እና ከታወቀ ሕንጻ ተቋራጭ ጋር በመዋዋል ወደግንባታ በመግባት ላይ ካለ አዲስ የ14-ፎቅ ሕንጻ ባሻገርም በሁለት ከተሞች ላይ የቀጠናዊ ጽ/ ቤት ሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡  ከዕለት-ተዕለት ሥራና የባንክ እንቅስቃሴ ባሻገርም ባንካችን የሚጠበቅበትን ተቋማዊ ማኅበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አንጻር የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ለጋስ እጆቹን ሲዘረጋ ቆይቷል፡፡

በቀጣይ፣ እራሳችንን ይበልጥ አስተማማኝና ጥሩ መሠረት ወዳለው ባንክ ከመቀየር አንጻርም በቁርጠኝነት እና ተግዳሮቶችን በመቋቋም መንቀሳቀስ አማራጭ የሌላቸው መንገዶቻችን ናቸው፡፡  በአዲሱ የበጀት ዓመት ለምናካሂደውና ሙሉ ዝግጅቱ ለተጠናቀቀው የባንካችን መሪ-ዕቅድ ዝግጅት ፕሮጀክትም ባንካችንን ከነባራዊውም ሆነ ከፊታችን ከሚታዩን መሰናክሎችና ችግሮች ውስጥ ሊያሻግር የሚችል የስራ ሞዴል ለመዘርጋት በከፍተኛ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡

የማኔጀመንት አባላትና መላ ሠራተኞች የባንካችንን እድገት እና ትርፋማነት ከማስጠበቅ አንጻር ላደረጉት ጥረት ተገቢው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡  በባንካችን ባለድርሻ አካላት በተደረገው ርብርብ በንብረትና ጥሬ ገንዘብ እንዲሁም በስራ መቋረጥ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳት በመቋቋም በአፋጣኝ አገልግሎት መስጠት ወደምንችልበት ቁመና ለመመለስ ችለናል፡፡  ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ለምናገኘው ድጋፍና ትብብር ሁሌም ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን፡፡  አሰራራችንን ለማሻሻል ለምናደርገው ያላሰለሰ ጥረት ዋነኞቹ ምክንያት በሆኑትና ሁሌም ወደፊት እንድንራመድ በሚረዱን ውድ ደንበኞቻችን በጣሙን እንኮራለን፡፡  የባንክ ዘርፉን ጤነኛና የተረጋጋ ከማድረግ አንጻርም በመንግስትና ተቆጣጣሪ አካላት እየተወሰደ ያለውን መልካም እርምጃ ሳንጠቅስ ማለፍ አንወድም፡፡

አመሰግናለሁ!

ኢትዮጵያ ታደሰ

የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር