የዋና ሥራ አስፈጻሚ መልዕክት

ውድ የባንካችን ባለአክሲዮኖች፣

 

ያለፈውን የበጀት ዓመት የባንካችን የሥራ አፈፃፀም ለመገምገም  በድጋሚ በመገኛኘታችን የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

የ2015 ዓ.ም ከዓለም አቀፍ መድረክ አንስቶ እስከ ሀገራዊ ከባቢዎች ድረስ እንደምታ በነበራቸው ተግዳሮቶች የታጀበና በበርካታ አሉታዊ ሁነቶች የሚጠቀስ ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡ ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰው የራሺያ-ዩክሬን ግጭትም በዚህም ዓመት ያልተቋጨ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከአየር ጠባይ ለውጥ ጋር ተያይዞ ዓለማችን አስከፊ የተፈጥሮአዊ ቀውሶችን እና አደጋዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡

የዋጋ ንረቱ ከፍላጐት እና አቅርቦት አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ ከፍ ብሎ የቆየ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ ተስተውሏል፡፡ የዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም /IMF/ ሪፖርት እንደሚያሳየው የዓለም የኢኮኖሚ እድገት እ.ኤ.አ. በ2022 ደካማ የነበረ ሲሆን የ3.5 በመቶ የዕድገት ምጣኔ አስመዝግቧል፡፡ እ.ኤ.አ. የ2023 ትንበያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቅናሽ እያሳዩ ሲሆን የቅርብ ጊዜው ግምት የ3 በመቶ ምጣኔን ያመላክታል፡፡

በአፍሪካም የተስተዋሉት የዕድገት ተግዳሮቶች በዓለምአቀፍ ደረጃ ከታዩት የተለዩ አልነበሩም፡፡ በርካታ ሀገራት በተለያዩ ቀውሶች ሲናጡ ቆይተዋል፡፡ በዋነኛነትም የራሺያ- ዩክሬን ግጭት፣ የሸቀጦች ዋጋ መናርና የምግብ እጥረት፣ አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች እና የዕዳ ጫናዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በተለይ ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ጠቅላላ ምርት የዛሬ ዓመት ከተመዘገበው የ4.1 በመቶ የዕድገት ምጣኔ ወደ 3.6 በመቶ ዝቅ ሊል ችሏል፡፡ እ.ኤ.አ. የመጪው 2023 ትንበያም ተጨማሪ ቅናሽ እንደሚያስመዘግብና ወደ 3.1 በመቶ እንደሚወርድ ይጠበቃል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ሸምጋይነት የተካሄደውን ስምምነት ተከትሎ ከሁለት ዓመት የሰሜኑ ግጭት በኋላ ወደ ሰላማዊ ጉዞ ተመልሳለች፡፡ ምንም እንኳን የበጀት ዓመቱ በተግዳሮቶች የታጀበ ቢሆንም ኢኮኖሚው አምና ካስመዘገበው የ6.4 በመቶ ዕድገት ወደ የ7.5 በመቶ ከፍ ማለቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሶስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚው ዘርፎች የታየውን እንቅስቃሴም ስንመለከት በኢንዱስትሪ እና የግብርና ዘርፎች ከታየው አነስተኛ ቅናሽ አንጻር በአገልግሎት ዘርፍ መጠነኛ ጭማሪ ተመዝግቧል፡፡

የባንክ ኢንዱስትሪው የመንግስት ባንኮችን ጨምሮ የተሳታፊዎቹን ብዛት 29 በማድረስ ሰፊ የውድድር መድረክ ሆኗል፡፡ በዓለምአቀፍ እንዲሁም በሀገር ውሰጥ የተከሰቱ መጠነ-ሰፊ ችግሮችን በመቋቋም ዘርፉ በሁሉም ዋና ዋና መመዘኛዎች ማለትም እንደ ተቀማጭ ገንዘብ፣ ካፒታል፣ የአገልግሎት ተደራሽነት፣ እንዲሁም ትርፍ አንፃር ዕድገት ማስመዝገቡን ማስቀጠል ችሏል፡፡

ባንካችን ዓባይ ከሁሉም አበይት መመዘኛዎች አንጻር አበረታች ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን የ29 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት በማስመዝገብ ብር 41.8 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ አዳዲስ ደንበኞችን ከማፍራት አኳያ የደንበኞቻችን ቁጥር የ49 በመቶ ዓመታዊ ዕመርታ በማሳየት 2.5 ሚሊዮን በማድረስ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ አዳዲስ አካባቢዎችንም በማሰስ በመላ ሀገሪቱ በአጠቃላይ 110 አዳዲስ ቅርንጫፎች የተከፈቱ ሲሆን ይህም ከባንኩ ምስረታ አንስቶ ከፍተኛው ዓመታዊ ዕድገት ነው፡፡

ገቢን ከማሳደግ እና ወጪዎቻችንን ከመቆጣጠር አንፃር ያከናወናቸው አጠቃላይ የውጤታማነት አድማስን የማስፋት ሥራ አዲስ የትርፋማነት ከፍታ እንድናስመዘግብ አስችሎናል፡፡ በዚሁም መሠረት ጠቅላላ ትርፋችን ከታክስ በፊት ብር 2.1 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ከባለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ የ63 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ባንካችን ተገቢውን የብድር ሂደቶች እና ዲሲፕሊን የተከተሉ አሠራሮችን ከመተግበሩ ጋር ተያይዞ በዓመቱ ውስጥ የተመዘገበው የታማሚ ብድር ምጣኔ ከኢትየጵያ ብሔራዊ ባንክ ዝቅተኛ ምጣኔ አንጻር በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የባንካችንንም ዕሴቶች እንዲሁም ተልዕኮ በሚያንጸባርቅ መልኩም ባንካችን ለተለያዩ ማኀበረሰቦች በርካታ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ባንካችን ለበርካታ ወገኖች ለጋሽ እጆቹን በመዘርጋት እስከ ብር 34.6 ሚሊዮን የሚደርስ ገንዘብ ለግሷል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት በባንካችን ከተከናወኑ ዓበይት ጉዳዮች መካከል Aጉዞ ከፍታ” የተሰኘው የአምስት ዓመት የመሪ ዕቅድ ዝግጅት ይገኝበታል፡፡ አዲሱ መሪ ዕቅድ በውጭ አማካሪ በታገዘ በባንኩ የውስጥ ዓቅም የተዘጋጀ ሲሆን ከ2016 እስከ 2021ዓ.ም. ድረስ የምንጓዝበት ይሆናል፡፡ ይህንንም ወሳኝ ሥራ ተከትሎ ባንካችን የመሪ ዕቅዱ የቅድመ-ትግበራ ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ በዚሁም መሠረት የሥራ ሂደቶችን በማሻሻልና እመርታ በማምጣት መሪ ዕቅዱን በበቂ ሁኔታ መደገፍ የሚያስችል አዲስ የመዋቅር ጥናት በማካሄድ ወደ ስራ የገባ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የሰው ኃይል ምደባ ተጠናቅቋል፡፡ የባንካችንን ብራንድ ጉልህነት እንዲሁም አጠቃላይ ዕይታ የማሻሻል /ሪብራንዲንግ/ ሥራም ተጀምሯል፡፡

በቀጣይም በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ በመጓዝና ተግዳሮቶች በመቋቋም ለግቦቻችን ስኬት በጽናት በመስራት ለተሻለ ውጤታማነት እንተጋለን:: አዲሱን ዓመትም ከተለምናቸው ግቦች የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የምንጥርበት ዓመት ይሆናል፡፡

በዚህ ዓመት ለተመዘገበው ውጤት ከጐናችን ለነበሩት ባለድርሻ አካላት ሁሉ ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ ከሁሉ አስቀድሜ ጠንካራ የስራ መነሳሳት ላሰረጹብን የባንካችን የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት እንዲሁም የስራ ጊዜያቸውን ፈጽመው በክብር ለተሰናበቱ የቀድሞው ቦርድ አባላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና እገዛ ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በተጨማሪም የባንካችን የሥራ አመራር አባላትና ሰራተኞች ላሳዩት ትጋትና ታታሪነት እንዲሁም ጥብቅ በሆነ የአብሮነት ጉዞ ከባንካችን ጋር ለተቆራኙት ውድ ደንበኞቻችንና ባለአክሲዮኖች የከበረ ምስጋናየን እያቀረብኩ ዘወትር በተሻሻሉ አገልግሎቶቻችን ደንበኞቻችንን ለማርካት ቃል በመግባት ጭምር ነው፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት ከማስጠበቅና ባንኩን ከመደገፍ አንጻር ላደረገልን አስተዋጽኦ ልባዊ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡

 

አመሰግናለሁ!

የኋላ ገሠሠ

ዋና ሥራ አስፈጻሚ