የዓባይ ባንክ ሠራተኞች በዛሬው ዕለት በሰሜን ወሎ ዋግህምራ እና ሰቆጣ አካባቢዎች በድርቅና ረሀብ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ የሚሆን ጠቅላላ ዋጋው ብር 4,000,000 (አራት ሚሊዮን ብር) የሆነ፣ ብዛቱ 1,000 ኩንታል የምግብ ዱቄት በዕርዳታ ለተጎጂዎች ይደርስ ዘንድ ለአማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ-ኢትዮጵያ) አስረክበዋል።

የባንኩን ሠራተኞች በመወከል የተደረገውን ድጋፍ ለአመልድ-ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አሰፈጻሚ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ በባህርዳር ከተማ አመልድ-ኢትዮጵያ ዋና መ/ቤት በመገኘት ያስረከቡት የዓባይ ባንክ ስትራቴጂና ማርኬቲንግ ዋና መኮንን የሆኑት አቶ ወንድይፍራው ታደሰ ናቸው።

አመልድ ኢትዮጵያ ከዓባይ ባንክ ያገኘውን የእለት እርዳታ ለሰቆጣ ተፈናቃዮች እንደሚያሰራጭ የተገለፀ ሲሆን ፣ በተደረገው ድጋፍ የተገኘውን 1 ሺህ ኩንታል የስንዴ ዱቄት ተፈናቅለው በዋግኸምራ ዞን ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖች ለማድረስ ወደ ቦታው እያጓጓዘ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አሰፈጻሚ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ እርዳታውን ከዓባይ ባንክ ሲረከቡ እንደገለጹት በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ውስጥ ከ11.6 ሚሊዮን በላይ እርዳታ የሚያስፈልገው ህዝብ መኖሩን አውስተው የዓባይ ባንክ እና ሰራተኞቹ በረሃብ ለተጋለጡ ወገኖቻችን ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.