የባንካችን ታሪክ

አጠቃላይ እይታ

የኢትዮጵያ ውብ ፈርጥና የኩራት ምንጭ የሆነው ታላቁ ዓባይ ወንዝ ልዩ መስእብን የተጎናፀፈ የተፈጥሮ ፀጋ ከመሆኑም ባሻገር ለሀገራችን ቀጣይ ልማትእምቅ ጉልበት ያለው ወንዝ መሆኑንበተግባር እያስመሰከረ ይገኛል፡፡ባንካችንም ‹‹ዓባይ›› የሚለውን ስያሜ ያገኘው ከዚሁ ታላቅና ከፍተኛ ጉልበት ካለው ወንዛችን ባህሪ በመነሳት ሲሆን ባንካችን ታማኝ የደንበኞች አገልጋይ በመሆን ደኅንነቱ የተረጋገጠ እናአስተማማኝ የሆነ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የካፒታል ክምችትን በማዳበር የስራ እድልን የሚፈጥሩ የተለያዩ ዘርፎችን በፋይናንስ በመደገፍ ዕድገትን እያፋጠነ ይገኛል፡፡

የዓባይ ወንዝን ለመጎብኘት ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶች አካባቢውን እና የነዋሪዎቹን አቀባበል በልዩ መደመም እና በደስታ እንደሚመለከቱ ሁሉ፣ የባንኩ ትጉህና ቀልጣፋ ሠራተኞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በፍጥነትና በቅልጥፍና በማስተናገድ ደስታን ያጎናፅፉዎታል፡፡ ዓባይ ባንክ የኢትዮጵያ ፈርጥ የሆነው የዓባይ ወንዝ በቀጣይ ለሚኖረው የሀገሪቱ ዕድገት የጎላ ሚና እንደሚጫወተው ሁሉ፣ ባንካችን ደግሞ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ለአርሶ አደሩ፣ ለአምራች ማኅበራት፣ ለንግድ ተቋማት እንዲሁም ከባንኩ ጋር ለሚሠሩ ደንበኞች ፈጣን ዕድገትና ልማትን የመፍጠር ራዕይን ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የዓባይ ባንክ አመሰራረት

ዓባይ ባንክ አ.ማ. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚጠይቀውን መስፈርት በማሟላት ሐምሌ 7 ቀን፣ 2002 ዓ.ም.የተመሠረተ ሲሆን፣ በይፋ ሥራውን የጀመረው ጥቅምት 25 ቀን፣ 2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ባንኩ ሲመሠረት በብር 174.5 ሚሊዮን የተፈረመ ካፒታልና በብር 125.8 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል፣ በ823 መስራች አባላት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ  ሰኔ 30/2023 ድረስ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ብር 4.733/  አራት ቢሊየን ሰባት መቶ ሠላሣ ሶስት ሚሊየን ብር / የደረሰ ሲሆን የባንኩ ባለአክሲዮኖችም ቁጥር 4,437/ አራት ሺህ አራት መቶ ሰላሳ ሰባት/ ደርሷል፡፡

ዓባይ ባንክ ለሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የተቀላጠፈ አገልግሎትበሁሉም ቅርንጫፎቹ እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ የሀገር ውስጥ ንግድ እና አገልግሎት፣ ዓለም አቀፍ ንግድ፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ትራንስፖርት፣ ግንባታ፣ ሪል ስቴት እናሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ዓባይ ባንክ ሁሉንም የንግድና የሥራ ዕድሎችን በመጠቀም የእያንዳንዱን ቢዝነስ የገንዘብ ጥያቄና ፍላጎት በማሟላት ተመራጭ የሥራዎ አጋር ለመሆን አቅሙን አጎልብቶ በመሥራት ላይ ይገኛል። ባንኩ በሴክተሩ ላይ የሚታየውን የፋይናንስ አገልግሎትና አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ድልድይ በመሆን የራሱን ትልቅ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

ዓባይ ባንክ በሁሉም ደረጃ መልካም ስኬቶችን ተጎናጽፏል። ባንኩ ሥራ በጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመላው ሀገሪቱ በርካታ ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከ487 በላይ በማድረስ ተደራሽነቱንና ህዝብ አገልጋይነቱን ይበልጥ ለማሳየት ችሏል፡፡ በዚሁ መሠረት እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 30/2023 ድረስ 2,509,638 (ሁለት ሚሊየን አምስት መቶ ዘጠኝ ሺህ ስድስት መቶ ሰላሳ ስምንት) በላይ ደንበኞች በባንኩ ሒሳብ ከፍተው በመገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡