ዓባይ ባንክ እና የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ሕብረት የጋራ ሥራ ስምምነት ተፈራረሙ

ዓባይ ባንክ እና የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ሕብረት የጋራ ሥራ ስምምነት ተፈራረሙ

ዓባይ ባንክ አ.ማ. ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ሕብረት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ሕብረት አባላት እና ሠራተኞች በባንኩ በመቆጠብ የቤት እና መኪና መግዣ እንዲሁም ለተለያዩ ጉዳዮች የሚያስፈልጋቸውን ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል ይሆናል፡፡

ስምምነቱን የዓባይ ባንክ ተጠባባቂ ዋና – ሪቴል ባንኪንግ መኮንን አቶ ማርቆስ ደመቀ እና የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ሕብረት ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ ተፈራርመዋል፡፡

አቶ ማርቆስ ደመቀ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር አባላቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ከዓባይ ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ማድረጉ የሚያስመሰግነው ሲሆን፣ አርቲስቶች በተለይ የቁጠባ ባህላቸውን በማጎልበት ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ዕድል እንደሚፈጥርላቸውም ገልጸዋል፡፡

አቶ ዳዊት ይፍሩ በበኩላቸው በሙዚቃ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አርቲስቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ ቢሆኑም፣ በተደራጀ መልኩ በፋይናንስ አቅም ተጠቃሚ ባለመሆናቸው በቀጣይ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥላቸው ዕድል ስለተመቻቸላቸው ዓባይ ባንክን አመስግነዋል፡፡

በፊርማ ሥነ – ሥርዓቱ የማህበሩ አባላት አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ፣ አርቲስት ኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ)፣ አርቲስት ሄኖክ መሀሪ፣ አርቲስት አቤል ሙሉጌታ፣ የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳን ጨምሮ የህብረቱ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

ዓባይ ባንክ አገልግሎቱን በማስፋፋት ደንበኞቹን የሚመጥኑ የተለያዩ አገልግሎቶችን እያቀረበ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ከኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ፣ ዳሽን ቢራ አ.ማ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ዋግ ልማት ማህበር፣ ያርድስቲክ ኢንተርናሽናል፣ ኑር ኢንተርናሽናል፣ አይኤፍ ዓለምአቀፍ የማዳበሪያ ልማት ማዕከል እና ከሌሎችም ድርጅቶች ጋር የብድር አገልግሎት በመስጠት ሠራተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.